የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ከባለፈው ሀገራዊ ምርጫ ድል በኋላ አዲሱ ካቢኔያቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ በአዲሱ ካቢኔያቸው ውስጥ ሴቶችን ጨምሮ አዳዲስ ሚኒስትሮችን እና የቀድሞ ፖለቲከኞችን አካተዋል ተብሏል።
ሲያወዛግብ የነበረውን የታንዛኒያ ምርጫ በማሸነፍ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው የበቁት ማጉፉሊ ቃለመሃላ ከፈፀሙ ከ 30 ቀናት በኋላ ነው አዲሱን ካቢኔያቸውን ይፋ ያደረጉት።
በሀገሪቱ ባመጧቸው በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተወዳጅነትን ያተረፉት ማጉፉሊ ምርጫውን 84 ከመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ከቀድሞ ሚኒስትሮች መካከል በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ በፕሬዝዳንቱ የተካተቱት የፋይናንስ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይገኙበታል።
ከመንግስት ምክር ቤት የተሰጠው መግለጫ እንደሚያሳየው የፋይናንስ ሚኒስትሩ ፊሊፕ ምፓንጎ ፖሊሲዎችን በማስቀጠል የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ በማድረጋቸው በፕሬዝዳንቱ እምነት ተጥሎባቸዋል።
እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፓላማጋምባ ካቡዲ ሀገሪቱ ከውጭ አጋሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብሏል።
አዲስ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት መካከል ፎስቲን ጉጉሊን በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ይመራሉ ነው የተባለው፡፡
የፕሬዝዳንት ፖምፔ ማጉፉሊ አዲሱ ካቢኔ በአጠቃላይ ሁለት የፓርላማ አባላትን ጨምሮ 23 ሚኒስትሮችን የያዘ መሆኑን አናዶሉ ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል፡፡