ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ትህነግ የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ ያለ ልዩነት በጋራ መቆም እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ለስምንተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ምልምል የልዩ ኀይል አባላት አስመርቋል፡፡
አቶ ገዱ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ወረራውን ለመቀልበስ እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ከተለያዩ አካባቢዎች ሁለገብ ኀይል ሰልጥነው ዘመቻውን በመቀላቀል ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ሀገር ለማፍረስ የተንቀሳቀሰውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋትና በሕዝቡ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ልዩነት ሳይገድበን በጋራ መመከት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ተመራቂ የልዩ ኀይል አባላት ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር ተቀናጅተው አሸባሪውን ቡድን እንዲደመስሱም መመሪያ መስጠታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ዘርፍ አማካሪ ክርስቲያን ታደለ በተመራቂ የልዩ ኀይል አባላት የታየው ወኔ እና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዳስደሰታቸው ተናግረው ይህም የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት ያስችላል ብለዋል፡፡