የትምህርት ሥርዓቱን በውጤታማነት ለመምራት የሥራ ባሕል ለውጥ ማምጣት አለብን – ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የማጠቃለያ እቅድ ግምገማ እና የ2015 ዓ.ም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የምክክር መድረክ በወልድያ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ፒኤችዲ) እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት ያለፈው በጀት ዓመት የክልሉ ሙሉ ትኩረት የኅልውና ዘመቻው ላይ እንደነበር ጠቁመው “አሸባሪው ትህነግ የፈጸመብንን ወረራ ለመመከት የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን አቁመን ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለናል” ብለዋል፡፡

ወረራው ከተቀለበሰ በኋላ የትምህርት ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት የተከናወነው ተግባር በበርካታ ፈተናዎች የታጀበ እንደነበርም ነው ያነሱት።

በወረራ ሥር የነበሩ የትምህርት ተቋማት ወድመዋል፣ ሰነዳቸው ጠፍቷል፣ ግብዓታቸውም ተዘርፏል ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ ባለው ውስን ሐብት ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ጥረት የትምህርት የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች አኩሪ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ሥራ ጀምሯል፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ የዘርፉ አመራር ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል ነው ያሉት።

አማራ ክልል በየዓመቱ በሚሰጡ ክልላዊና ሀገራዊ የትምህርት ፈተናዎች የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ካለፈው ዓመት ውጤት ተምረን የተሻለ የትምህርት ሥርዓት ለመገንባትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መሰማራት አለብን ብለዋል።

ትምህርት ሀገር የሚገነባ ትልቁ መሳሪያችን ነው፤ የተሻሻለው የትምህርት ሥርዓት በሙከራ ትግበራው የተሻለ አሠራሮችን ይዞ የመጣና በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች የሰጡት ግብዓት ተጨምሮበት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በትምህርቱ ዘርፍ የተማሪዎች ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት ርዕሰ መሥተዳድሩ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የተማሪ ወላጆችንና አጋር አካላትን በማሳተፍ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ፒኤችዲ) እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው መፈናቀልና የትምህርት ተቋማት ውድመት የ12ኛ ክፍል ላይ ያጋጠመው ሁለገብ ችግር ፈታኝ ነበር።

የተማሪዎች ውጤት መቀነስ፣ በክልልና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት መቀነስ፣ ማሳለስና ማቋረጥም በእጅጉ ጨምሯል ነው ማለታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ እስከ ጳጉሜን 4 የተማሪዎች ምዝገባ የሚካሄድ ሲሆን፤ከመስከረም ዐ2/2015 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው መስከረም ዐ9/2015 ዓ.ም ትምህርት የሚጀመርበት ቀን ነው።