ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) –
የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ህወሃት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የባሰ ዋጋ እንዳይከፍል ቆም ብሎ ሊያጤንና ሊመረምር እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ ገለጹ።መንግስት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበለትን የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት መቀበሉ የሚመሰገን ተግባር መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
አሸባሪው የህውሃት ቡድን በስልጣን በቆየባቸው ጊዜያት የትግራይ ህዝብን ለከፋ ችግር ዳርጎት እንደነበርም ነው ያስታወሱት።
ይህ አልበቃ ብሎት የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ለማጋጨት ብሎም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በርካታ ሴራዎችን ሲፈጽም ቆይቷል ብለዋል።
ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት እንዲነሳ ሲያከናውነው ከነበረው ተግባር በተጨማሪ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ክልሉን ወደ ከፋ ቀውስ መክተቱንም ነው ያነሱት።
የፌዴራል መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ካጠናቀቀ ማግስት ጀምሮ የትግራይን ህዝብ በመደገፍ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ተግባራትን ማከናወኑንም አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ ለረሃብና ችግር እንዳይጋለጥ መላው ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማስገባት፣ ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንዲሁም የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረግ ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሸባሪ ቡድኑ የተለያዩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት የትግራይ ህዝብ ይህን በቅጡ እንዳይገነዘብ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ህወሃት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የባሰ ዋጋ እንዳይከፍል ቆም ብሎ ሊያጤንና ሊመረምር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ህወሃት በፊትም ይሁን አሁን ህዝቡን ለራሱና ለአጋሮቹ መጠቀሚያ አደረገው እንጂ የትግራይ ህዝብ በድህነት ውስጥ በርካታ ችግሮችን ማሳለፉንም አስታውሰዋል።
የትግራይ ህዝብ ይህን ተገንዝቦ መከራና ችግር ያመጣበትን ቡድን የተሳሳተ አመለካከት ከመደገፍ እንዲቆጠብም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ዘገበው ኢዜአ ነው።