ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አሸባሪው ህወሃት እያደረሰ ያለውን ኢሰብዓዊ ድርጊት የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዝ ጠየቀ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ ለፌዴራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ እንዲተላለፍ ጥያቄ የቀረበው የዜጎችን ህይወት ከአደጋ ለመታደግ እንደሆነ አስታውሷል።
የፌዴራል መንግስቱ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል የተቋረጡ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶች እንዲጠገኑ የማድረግ ግልጽ አላማ ይዞ ሲሰራ እንደነበርም ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ ዓለም ዓቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያመለከተው መግለጫው፣ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመመካከርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት የሲቪል ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክቷል።
ለዚህ ጥረት መሳካት በመርህ ላይ የተመሰረተ ውይይት ከተለያዩ አካላት ጋር እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁሟል።
ይህም ሆኖ ግን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔውን ተከትሎ የፌዴራል የጸጥታ አካላት ከክልሉ ለቀው በመውጣታቸው የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ አስከፊ እንደሆነ ሪፖርቶች ማመልከታቸውን ገልጿል።
በተለይም የጊዜያዊ አስተዳደሩን የህይወት አድን ተልዕኮ ጥረት ሲያግዙ የነበሩ ዜጎች ራሱን የትግራይ መከላከያ ሃይል ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ግድያ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል።
ባለፉት ሰባት ወራት በራያ፣ በእንደርታ፣ መቀሌ/ኹሃ እና አዲግራት በበጎ ፈቃደኝነት ህዝብን ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው የታጣቂ ቡድኑ ዒላማ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በተጨማሪም ተሰደው የሚገኙ ዜጎችን ችግር ለመፍታት የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት መደናቀፉን ጠቅሷል።
ታጣቂ ቡድኑ በክልሉ እያደረሰ ባለው ጥቃትና ዘረፋ ለሰብዓዊ ድጋፍ የተደራጁ መጋዘኖችም ላይ በመፈጸሙ ሊያጋጥም የሚችለውን የረሃብ አደጋ ለመቀልበስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደናቅፍም አስጠንቅቋል።
የአሸባሪ ቡድኑና ደጋፊዎቹ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስደት እየዳረገ መሆኑን የጠቆመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ ብዙዎች ለህይወታቸው በመስጋት እየተሰደዱ እንደሆነ ገልጿል።
የፌዴራል መንግስትም በቡድኑ አማካኝነት በየዕለቱ ለስደት እየተዳረጉ ያሉ ዜጎችን እየመዘገበ እንደሆነ ስለመሆኑ ጠቅሷል።
ወደ ኤርትራም እየተሰደዱ ያሉ ዜጎች መኖራቸውን ገልጿል።
በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ አጠቃላይ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ራሱን የትግራይ መከላከያ ሃይል ብሎ የሚጠራው አሸባሪው ህወሃት እያደረሰ ያለውን ኢሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝ ጊያዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል።
ቡድኑ ሊመጣ ከሚችለው የሰላም አማራጭ በተቃራኒ የሚያደርገውን ያልተቋረጠ የጠብ አጫሪነት ጥሪ መላው የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ እንዲገነዘበበውም አመልክቷል።
ህብረተሰቡም ለሰላም አማራጭ ትኩረት እንዲሰጥ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ማስገንዘቡን ኢዜአ ዘግቧል።