የቶኪዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው

የቶኪዮ ኦሎምፒክ መክፈቻ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – የመላው አለም ስፖርት አፍቃሪዎች በጉጉት የሚጠብቁት የቶኪዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡

ከ205 ሀገራት የተወጣጡ ከ11 ሺህ በላይ አትሌቶች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለተመልካች በሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ ቶኪዮ መግባታቸው ተገልጿል፡፡ በመክፈቻው መርሃ-ግብር ላይም ቢሆን ምንም ተመልካች እንደማይገኝ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ኦሎምፒኩ በይፋ ከመከፈቱ በፊት የተጀመሩት ውድድሮች ዛሬም ቀጥለው ይደረጉበታል፡፡

በውድድሩ ለአሸናፊዎች 5 ሺህ የተለያዩ ሜዳሊያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ለኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ሲባል አሸናፊዎች እንደቀድሞ ሜዳሊያቸውን ከክብር እንግዳ እጅ ሳይቀበሉ ከተዘጋጀበት ቦታ ራሳቸው እያነሱ እንዲያጠልቁ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ያለ ተመልካች በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተወዳዳሪ አትሌቶች በየቀኑ የኮቪድ ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለኦሎምፒክ ዝግጅቱ ከ14.8 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡