የኅዳሴ ግድብ ቀሪ የግንባታ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም የሰፊውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ እና ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል – ምጠ/ሚ ደመቀ

ደመቀ መኮንን

ማጋቢት 24/2014 (ዋልታ) የኅዳሴ ግድብ ቀሪ የግንባታ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም የሰፊውን ማህበረሰብ ተሳትፎ እና ድጋፍ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርሩ የታላቁ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዕለት አስመልክተው ያስተላለፉት ሙሉ ምልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለመላው ኢትዮጵያውያን!

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ለተጣለበት 11ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዕለት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ እንኳን አብሮ አደረሰን።

እነሆ! . . . ለሺሕ ዓመታት ሲፈስ የነበረው የዓባይ ወንዝ ለሃገራችን ሁነኛ የልማት አቅም ለመሆን በሩ የተከፈተበትን ታሪካዊ ዕለት በጋራ ለመዘከር አበቃን!

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ግድቡ ወሳኝ የግንባታ ሂደቶችን በማለፍ በአሁን ጊዜ የቅድመ~ሃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በዚህ ታሪካዊ የግንባታ ጉዞ የህዝባችን ሁለገብ ድጋፍ፤ የመንግስት ጠንካራ አመራር፤ የዲያስፖራ ወገኖቻችን እገዛ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ርብርብ በእጅጉ የሚደነቅ እና የሚያኮራ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ለደማቅ አበርክቷችሁ በመንግስታችን እና በመላው የሃገራችን ህዝብ ስም ከፍ ያለ ምስጋና እና አክብሮቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።

በቀጣይ ቀሪ የግንባታ ተግባራትን በውጤታማነት ለመፈፀም የሰፊውን ማህበረሰብ ተሳትፎ እና ድጋፍ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በሌላ በኩል በአሁን ወቅት በተለያየ መልክ የሚገለፁ ችግሮች ሃገራችንን እየፈተኗት ቢሆንም፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የተስተዋለውን የፀና ህዝባዊ አንድነት እና ህብረት የበለጠ አጠናክሮ በድል ማሻገር ይጠይቃል።

በመጨረሻም ከቀደሙ አባቶቻችን በወረስነውን የድል አድራጊነት ጠንካራ መንፈስ ለመጪው ትውልድ የታፈረች፣ የተከበረች እና የበለፀገች ሃገር ለማስረከብ አንድነታችንን እና ህብረታችንን አጥብቀን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

“ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን ነው!”

አመሰግናለሁ!