ጳጉሜን 5/2016 (አዲስ ዋልታ) የኋላ ታሪካችንን እያስታወስን የፊቱን መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሀመድ ሀሰን ገለጹ።
ኮርፖሬቱ በዛሬው ዕለት በተቋሙ ውስጥ በሚገኘው አረንጓዴ ስቱዲዮ በኢትዮጵያ ባለውለታዎች የተሰየሙትን ጨምሮ አራት በሮችን አስመርቋል።
በሮቹም ጳውሎስ ኞኞ በር፣ እሌኒ መኩሪያ በር፣ ሜጋ በር፣ እና ካሪቡ በር የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሀመድ ሀሰን፣ በአንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ፣ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ብሩክ ኃይሌ (ፕ/ር)፣ በአምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና በእሌኒ መኩሪያ ቤተሰቦች ነው ተመርቀው የተከፈቱት።
የኮርፖሬቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መሀመድ ሀሰን የሁሉም በሮች ስያሜ የኋላ እና የፊት ታሪክ እንዳላቸው አስረድተው የኋላ ታሪካችንን እያስታወስን የፊቱን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ያለፉት መልካም እና ምሳሌ የሚሆኑ ታሪኮቻችን እያስታወስን የወደ ፊቱን መገንባት አለብንም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ ስም የተሰየመው በር ለእኔ ልዩ ቦታ አለው ያሉት ዋና ስራአስፈፃሚው ምክንያቱም ሴቶችን ማክበር ሰውን ሁሉ ማክበር ነው፤ በዚህም እጅግ እኮራለሁ ብለዋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት አንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ አዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን የጥበብ ስራዎች የሚሠሩበትና የሚተላለፍበት ጥሩና ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ በመሆኑ ለተቋሙ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ብሩክ ኃይሌ (ፕ/ር) በበኩላቸው የአዲስ ዋልታ አረንጓዴ ስቱዲዮ ወጣት ትውልድን ማመንጫ መድረክ እንደሚሆን አምናለሁ፤ ዋልታ ወደፊት ብዙ እሌኒ መኩሪያዎችን እና ብዙ ጳውሎስ ኞኞዎችን እንዲያፈራ እንጠብቃለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእሌኒ መኩሪያ ቤተሰቦችም እሌኒን አስታውሶ ታሪካዊ በርን ላቆመላት ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአዲስዓለም ግደይ