“የነገ ተስፋ ህፃናት ለአዲስ አበባ” የተሰኘው የልጅነት እድገት ፕሮግራም ተጀመረ

መጋቢት 18/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር “የነገ ተስፋ ህፃናት ለአዲስ አበባ” የተሰኘውን የልጅነት እድገት (Early Childhood Development) ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ተጀመረ።
በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ሚንስትሮች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና፣ አጋር ድርጅት አመራሮችና የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር ተገኝተዋል።
የነገ ተስፋ የሆኑትን ህጻናት ሁለንተናዊ እንክብካቤና እድገት እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ነው። ይህን ለማስፈጸም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተዘጋጁትን የህጻናት ማቆያ፣ የህጻናት መጫወቻዎችና መናፈሻን ጤና ጣቢያዎችና የቤት ለቤት እንክብካቤ ጉብኝት ተደርጓል።
በሃገር አቀፍ ደረጃም መልካም ስብዕና ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ዜጎች ለማፍራት ትግበራውን ለማጠናከር በተከለሰው ፖሊሲ ላይም ውይይት አድርገናል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ለፕሮግራሙ መሳካት እየሰሩ የሚገኙ አመራሮች፣ ሰራተኞችና አጋር ድርጅቶችን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።