የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊነት

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት አኳያ እንዲሁም ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት በሚደረገው አገራዊ ጥረት ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ተናገሩ፡፡

የፌዴራልና የክልል ህብረት ስራ ማህበራትን የ2013 ተግባራትን በመገምገም በ2014 እቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በመድረኩ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የሚደረገውን አውደ ውጊያ ከመደገፍ ባሻገር በኢኮኖሚያዊ አሻጥር ምክንያት በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የሸቀጦች የዋጋ ንረት ለመከላከል መንግስት እየወሰደ ካለው መጠነ ሰፊ እርምጃ ጎን ለጎን ህብረት ስራ ማህበራትም የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ህብረት ስራ ማህበራት የከተማ – ገጠር የአምራች ሸማች ትስስርን በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ ለመስራት የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አኳያ በዘላቂነት መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ለማሳካትም ባለፈው በጀት ዓመት ጥሩ ስራ እንደተሰራና በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡ ዘገባው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው፡፡