የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰምድር እንፋሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት የምርት ሙከራ በይፋ ጀመረ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) የአሉቶ የከርሰምድር እንፋሎት ፍለጋ ቁፋሮ ከተጠናቀቀባቸው አራት ጉድጓዶች መካከል አንደኛው የምርት ሙከራ በይፋ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ መሳይ ፍቃዱ እንደገለፁት የአምስተኛው ጉድጓድ ቁፋሮ ሰባት መቶ ሜትር ላይ ደርሷል፡፡

ግንቦት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰምድር እንፋሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስድስተኛውን የእንፋሎት ፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማስጀመር የመቆፈሪያ ማሽን ወደቦታው በማንቀሳቀስ የመትከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር በአማካይ እስከ 75 ቀናት ይፈጃል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ቁፋሯቸው ከተጠናቀቁት አራት ጉድጓዶች መካከል የሁለተኛውን ጉድጓድ የምርት ሙከራ ሥራ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይጀመራል ብለዋል፡፡

የእንፋሎት ፍለጋ የጉድጓድ ቁፋሮው ወደ ከርሰምድር እስከ 3 ሺሕ ሜትር ጥልቀት የሚኖረው ሲሆን ፕሮጀክቱ እስከ 70 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW