መስከረም 21/2014 (ዋልታ) አዲሱ የአማራ ክልል መንግሥት መዋቅር የአማራን ሕዝብ ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ እንዲሰራ የሚያስችል ነው ሲል ክልሉ አስታወቀ።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ስለአዲሱ የክልሉ መንግሥት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በአዲስ መልኩ የተዋቀረው የክልሉ ካቢኔ የክልሉን ሕዝብ ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
75 በመቶ በአዲስ የተተኩት የአማራ ክልል ካቢኔዎች በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በዕድሜያቸውም ሆነ በሥነ ምግባራቸው ብቁ በመሆናቸው ክልሉ የገጠመውን ዘርፈ ብዙ ችግር ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
አዲሶቹ ተሿሚዎች የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን አደጋ የመቀልበስና የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል እውቀት እና ችሎታ ያላቸው መሆናቸውን ስለመግለፃቸውም የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።