የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል በሕጻናትና ሴቶች ላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው በነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አርብቶ አደሮች ላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር አስከባሪ በሆነው የአፋር ሕዝብ ላይ በአሸባሪው ሕወሓት የተፈጸመው ወረራና ጭፍጨፋ በአደጋው ልክ ምላሽ ካልተሰጠው በሌሎች ኢትዮጵያዊንም እንደሚደርስ ታውቆ አሸባሪውን ቡድን በጋራ ክንድ ወደመቃብር ለማውረድ ሁሉም እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመግለጫው ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-
ሐዘናችሁ ሐዘናችን ነው!
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው የነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አርብቶ አደሮች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አስመልክቶ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከዛሬ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በክልሉ የሐዘን ቀን እንዲሆን አውጇል።
በተጨማሪም በመጋዝን ተከማችቶ የነበረ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ይህን ታሪክ የማይረሳው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የአፋር ሕዝብን ብቻ ሳይሆን የክልላችንን መንግሥትና ሕዝብ በእጁጉ ያስቆጣና የህልውና ትግሉን አጠናክረን ከመቀጠል ውጭ አማራጭ እንደሌለን የሚያስገድድ ነው፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ሕዝብ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ በንጹሐን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የተሰማውን መሪር ሐዘንና ቁጭቱን ይገልጻል።
በወንድም የአፋር ሕዝብ ላይ የተፈጸመው የንጹሐን ጭፍጨፋ ለዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ እንደተፈጸመ፣ ባለፈው ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም. በማይካድራ በአማራ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን በማስታወስ፣ ይህ የሽብር ቡድን ጨርሶ ወደመቃብር እስካልወረደ ድረስ በሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ላይ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ የሚፈጽም በመሆኑ፣ በመላ የኢትዮጵያ ልጆች የተባበረ ክንድ ሊደመሰስ ይገባል።
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ግልጽ ጦርነት ስለማወጁ በአፋርና በአማራ ክልል እየፈጸማቸው ያሉ ጭፍጨፋዎች፣ አስገድዶ መድፈር፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ውድመት፣ የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ዘረፋዎች ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው። እነዚህ አውዳሚ ተግባራቱ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን በእልህና ቁጭት የጋራ ጠላታቸውን እንዲደመስሱ የሚያነሳሱ ናቸው እንጅ መቼውንም ለአሸባሪና ወራሪ ተጨማሪ የጥፋት ዕድል አንድንሰጥ የሚያደርጉን አይደሉም፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ውድ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በያሉበት ሆነው እንዲቃወሙና እንዲያወግዙ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥሪውን ተቀብሏል። የወንድም አፋር ሕዝብን መሪር ሐዘን መጋራት ብቻ እንደማይበቃም ያምናል። ሐዘንን ከመጋራት ባሻገር የጋራ ጠላታችንን በፍትሐዊ ጦርነት እናሸንፈዋለን፡፡
የእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳር ድንበር አስከባሪ የሆነው የአፋር ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወረራና ጭፍጨፋ በአደጋው ልክ ምላሽ ካልተሰጠው በሌሎች ኢትዮጵያዊንም እንደሚደርስ ታውቆ ይህን ቅጥረኛና ሀገር አፍራሽ ወራሪ ቡድን በጋራ ክንዳችን ወደመቃብር ለማውረድ መላ ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንዳንቸውን ማንሳት እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን፡፡
ሐዘናችሁ ሐዘናችን ነው!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም
ባሕር ዳር – ኢትዮጵያ