የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት

መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው 10ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የመስተዳድሩ ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የሚከናወኑ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ወጪያቸውን መሸፈን ላልቻሉ ወረዳዎች የበጀት ድጎማን በሚመለከት፣ ለልማት ተነሽ ለሚሆኑ ባለመሬቶች የሚከፈል ባሕር ዛፍ ካሳ ክፍያ፣ የርዕሰ መምህራን፣ ምክትል ርዕሰ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች ምልመላና መረጣ እንዲሁም የሥራ ስምሪትና የደረጃ ዕድገት በሚመለከት በቀረቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ምክር ቤቱ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚከናወኑ ወቅታዊ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን እንዲሁም የክልሉን ሰላምና ልማት በሚያረጋግጡ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይም የመስተዳድሩ ምክር ቤት የጋራ አቋም ላይ መድረሱን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW