የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ አካባቢዎች ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ እየተካሄደ ነው

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ማህበረሰብ ልዩ ዞን አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ መደፍረስ ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በዛሬው እለት በሸዋሮቢት ከተማ በተካሄደው የህዝብ ለህዝብ መድረክ የአማራ፣ ኦሮሞና ሌሎች ማህበረሰብ ነዋሪዎች የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ምክክር አድርገዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ለዘመናት የቆየውን የአማራና ኦሮሞ ማህበረሰብ ግንኙነት አይወክልም ብለዋል።
በመሆኑም በጋብቻ፣ በሀዘን፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የተሳሰረውን ማህበረሰብ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ይህ አይነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፋይዳው ከፍተኛ ነው ተብሏል።
አሁን የሰፈነው ሰላም እንዲፈጠርም የአሁኑን መድረክ ጨምሮ ስድስት እርቀ ሰላም መድረኮች እንደተከናወኑ ተገልጿል።
በፅንፈኛ ሀይሎች ጥቃት ተቋርጦ የነበረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተገለፀው።
(በደምሰው በነበሩ)