የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የማጠቃለያ የምርጫ ቅስቀሳውን በባህርዳር እያካሄደ ነው

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ፅህፈት ቤት የማጠቃለያ የምርጫ ቅስቀሳውን በባህርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በማጠቃለያ የምርጫ ቅስቀሳው ላይ የፓርቲው የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት ፓርቲው ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያካሄደው ቅስቀሳ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

የምርጫ ቅስቀሳው ኮሮናን ከመከላከልና የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ትንኮሳን ከመመከት ጎን ለጎን ተካሂዶ ውጤታማ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

ፓርቲው የህዝቡን  የልማት ጥያቄ በመለየት እልባት ከመስጠት ባለፈ ለዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያግዙ የልማት ሰራዎችን መጀመሩን ተናግረዋል።

“የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲቻል ህዝቡ ብልጽግና ፓርቲን ይምረጥ ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።