የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የምክክር መድረኩ ዓላማ የክልሉን አመራር ለቀጣይ ተልዕኮ ማዘጋጀት እና ማብቃት ነው ተብሏል፡፡

ክልሉ ለወራት በዘለቀው ወረራ ማኅበራዊ፣ ምጣኔሃብታዊ እና ፖለቲካዊ መዛነፎች ተፈጥረዋል ያሉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከዚህ ዘርፈ ብዙ ፈተና በፍጥነት ለመውጣት ወጥ አቋም ያለው፣ በቆራጥነት የሚሠራ እና ሕዝብን የሚያገለግል የአመራር ሥርዓት መዘርጋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ከችግሮቻችን በፍጥነት ለመውጣት ተከታታይ ምክክር፣ ውይይት እና ስልጠና ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የጋራ አቋም፣ ወጥ እሳቤ እና ተቀራራቢ አፈፃፀም አሁን ካለው አመራር የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው የክልሉ ሕዝብ ሥራ አስፈፃሚ ከሕዝቡ ጋር መነጋገር፣ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እና በተግባር የተገለጸ ችግር ፈች እርምጃ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቂ ጊዜ ስለማይኖር ቀን እና ሌሊት ያለረፍት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ መሰረታዊ የሆኑ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ቁርጠኛ አቋም መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የቀጣይ ተልዕኮ በዚህ “የጊዜ የለንም መንፈስ” የተቃኘ ሆኖ እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን የኅልውና ጦርነት በተሟላ ድል የምታጠናቅቀው አፍራሽ አስተሳሰቦች ፈጽመው ሲከስሙ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ምጣኔሃብታዊ ትርጉም ያለው ዘርፈ ብዙ ነበር ያሉት አቶ ተመስገን አንጸባራቂ ድሎች ተመዝግበዋል፤ ድሉም የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ድል ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልል ወረራ ሲፈጽም የኢትዮጵያ መውጫ እና መግቢያ በሮች በመቆጣጠር ኅልውናዋን መገዳደርና ወደሚፈልገው ድርድር መምጣት፣ በሱዳን በኩል መውጫ ኮሪደር ማስከፈት፣ የአማራን ሕዝብ አንገት ማስደፋት እና ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደነበር ገልጸው የሽብር ቡድኑ በሁሉም ዘርፎች አልተሳካለትም ብለዋል፡፡

ከድል በኋላ ባሉ የድኅረ ድል መዛነፎችን ማረም እና የጋራ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ተመሥገን በችግሮች ላይ ሰፊ፣ ቀና እና በተግባር የተደገፈ ውይይት ከተደረገ መፍትሔዎቹ ቀላል ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ የጋራ ትብብር እና ሕዝባዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤ የምክክር መድረኩም በዚህ ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በምክክር መድረኩ ከፌደራል እስከ ወረዳ ያሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ ሲሆኑ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል አሚኮ ዘግቧል፡፡