የአሜሪካ ሀገራትን የማፍረስ ፖሊሲ

የአሸባሪዎች ጥቃት በአሜሪካ ሰማይ ስር በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር መስከረም 11 ቀን 2001 ተከሰተ፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ የዋሽንግተን የውጭ ፖሊሲ መልኩን እንደቀየረ በምዕራባውያኑ ይነገራል፡፡
ነገር ግን ዛሬም አጠያያቂ የሆነ ጉዳይ አለ፡፡ እርሱም ዋሽንግተን በአንድ በኩል የፀረ-ሽብርተኛ ዘመቻ አራማጅ በሌላ በኩል የሽብርተኞች ፈጣሪ እና ደጋፊ ስለመሆኗ አመላካች መረጃዎች በመኖራቸው ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመስከረሙ ጥቃት ከተፈፀመ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኮንግረሱ የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ‹ከእንግዲህ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ሽብርተኝነት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል› ሲሉ ተደመጡ፡፡
አክለውም “ከዲፕሎማሲ ስራችን እስከ እያንዳንዱ የህግ ማስፈጸሚያ ስርዓታችን፤ ከፋይናንስ አቅማችን እስከ ዳበረው የጦር መሳሪያችን የአለም አቀፍ ሽብርተኝነት ኔትወርክን ለማጥፋት ይውላል ነበር ያሉት፡፡
ከራስ ፍላጎትና ጥቅም የሚመነጨው ዛቻም አልቀረም አሜሪካም የውጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መጠኗን እያሰፋች መጣች፡፡ የመከላከያ ሰራዊቷን በከፍተኛ ወጪ መደጎም ጀመረች፡፡
የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን መከላከል በሚል ጦሯን በተለያዩ ሀገራት ማሰማራትንና ጣልቃ መግባት ተያያዘች፡፡ ይህ አካሄዷግን የራሷን ጥቅም ለማራመድ ነው በሚል በአንዳንድ ሀገራት ሲያስተቻት ቆይቷል፡፡
ይኽው መንገድ የአሜሪካ ውጭ ፖሊሲ ቀጣይነት የነጩ ቤተ መንግስት መገለጫ ሆነ፡፡ ይህንኑ አከሄድ አንዳንዶች የቡሽ ዶክትሪን ይሉታል፡፡ ነገር ግን ቀድሞም የነበረ ስለመሆኑ በ1950ዎቹ በኮሪያ የነበራት ሚና በማሳያነት ይነሳል፡፡
በመቀጠልም የዋሽንተን ሰብዓዊ እርዳታ የውጪ ፖሊስ ስትራቴጂ አካል ሆነው ብቅ አሉ፡፡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ተጠሪነቱ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሆነ፡፡ ተቋሙም ለዚሁ የውጭ ፖሊሲ ይበልጥ ተገዥ እንዲሆን ተደረገ፡፡ በወቅቱም አሜሪካም የሰበዓዊ ስራን የውጭ ጣልቃ ገብነት ማስፈፀሚያ በማድረግ ሰበዓዊነትን አረከሰች ብሏል የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ ስቲቭ ጆንስ፡፡
በአሜሪካ ሙሉ ስልጠና ሲሰጠው የነበረው የአልቃ-ኢዳው እርሾ ኦሳማ ቢላደን በፓኪስታን ለ 5 ዓመታት ተደብቋል መባሉ በመረጃ ሲታገዝ ዋሽንግተን ጦሯን በአፍጋን ጎሮቤት ፓኪስታን ላይ አዘመተች፡፡ ጣልቃ ገብነቱ በዚህም አላበቃም ይኽው መዘዝ ፊቱን ወደ አፍጋኒስታን አዞረ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የአልቃኢዳ አጋር ነው፤ ያለውን ታሊባንን ለመውጋት፤ በአፍጋኒስታን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አካሄደ፡፡
በአሜሪካ የሚመራው ጦር ለ20 ዓመታት ያህል ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአፍጋኒስታን አካሄዷል፡፡ የአሜሪካ ውክልና ያልተለየው በርካታ የተኩስ አቁም ውይይቶች በአፍጋንና ታሊባን መካከል ተካሂደዋል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ውጤት አልባ ነበሩ፡፡
ባለፈው ዓመት ግን የታሊባን የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫ በሆነችው ኳታር ዶሀ የተካሄደውን ድርድር በአንፃራዊነት የተሻለ መግባባት የታየበት ነበር ይላል አጃንስ ፍራንስ ፕረስ በዘገባው፡፡
የጆ ባይደን አስተዳደር ወደ ስልጣን በመጣ ጊዜ አፍጋኖች ትልቅ ተስፋን ሰንቀው ነበር፡፡ ነገር ግን በወራት ውስጥ ነገሮች መልካቸውን ቀይረው የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን እንዲወጣ አዘዙ፡፡ ጦሩ ከአፍጋኒስታን መልቀቁን ተከትሎ በመላው አገሪቱ አመጽ እንዲባባስ ሆኗል።
ታሊባን በከፍተኛ ፍጥነት በርካታ የአፍጋኒስታን አካባቢዎችን በመቆጣጠር በመዲናዋ ካቡል የሚገኘውን ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ወርሷል። ይሁን እንጂ አልጀዚራ የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ፣ ባለቤታቸው እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው ሀገር ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገር ኡዝቤኪስታን ኮበለሉ ።
ፕሬዘዳንቱም በፌስቡክ ገጻቸውባስተላለፉት መልዕክት በአገሪቱ ደም መፋሰስን ለማስቀረት በሚል ከባድ ውሳኔ በመወሰን አገር ጥለው መሰደዳቸውን ለአፍጋን ሕዝብ አረዱ።
አሁን የአፍጋኒስተን ዋና ከተማ ካቡል የፅንፈኛው ታሊባን መፈንጫ ሆና ሳለ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በአፍጋኒስታን ላይ ከወራት በፊት በወሰኑት ውሳኔ አንዳችም እንደማይፀፀቱ ተናግረዋል፡፡ እዚህ ጋር ለምን የሚል ጥያቄ መንሳቱ ተገቢ ነው፡፡
ጆ ባይደን በበዓለ ሲመታቸው ቀን ከቀሪው ዓለም ጋር የእድገት ፤ የሰላምና ደህንነት አጋር ለመሆን አሜሪካ ተመለሰች፤ የዶናልድ ትራፕ ሀገራትን የማግለል ፖሊሲ አክትሟል በማለት ተናገሩ፡፡
በአሜሪካ የስትራቴጂ መሀንዲስ ተብለው የሚወደሱት ኩርት ካምቤል የኢንዶ ፓስፊክ የተሰኘው የአራትዮሽ ህብረትን ቀየሱ፡፡
ጥምረቱ አውስትራሊያ አሜሪካ ጃፓን እና ህንድን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት በቻይና ሉዓላዊ ግዛት ዙሪያ የሚገኙ መሆናቸው እስትራቴጂው ዋሽንግተን የቻይናን የማይቀር የሀያልነት ጉዞ ለመግታትት የተሸረበ ሴራ መኖሩ ማጤን ይበጃል፡፡ ጆ ባይደንም ስልጣን በያዙ በ2 ወራት ውስጥ ነበር ይህንኑ ህብረት ሰብስበው የመከሩት፡፡
የሀገራቱ ህብረት ዋነኛ ግቡም እያደገ የመጣውን የቻይናን አቅም ማዳከም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የባይደን አስተዳደር በግልፅ ለሁሉም የኤሲያ ሀገራት እኩል አተያይ የለንም ብሏል፡፡ በዚህ አተያይ አሁን ላይ የቻይናን እንቅስቃሴ የመግታት ፕሮጀክት ውስጥ የአፍጋኒስታን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጥቅም አልባ እንደ ሆነ በዲሞክራቶቹ ታምኗል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ትልቁ ነጥብ አሜሪካኖቹ ማለቂያ የሌለው ብለው ከሚጠሩት የአፍጋኒስታን የእርስ በርስ ጦርነት እራሳቸውን ያገለሉት አፍጋኒስታን ከቻይና ጋር ድንበር የምትጋራ በመሆኑ ፅንፈኛው ታሊባን ቻይናን ለማሸበር ሁነኛ መጠቀሚያ ማድረግን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡
የግሎባል ታይምስ ዋና አዘጋጁ ሁ ሺጂን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሀላፊው ብሊንከን ከአፍጋን ህዝብ ጎን መቆም ለምን አልፈለጉም ሲል በሚጠይቀው የቲውተር ገፃቸው አስተያየት ምናልባትም የሴራው ማጠንጠኛ ቤጂንግ በመሆኗ ስራቸውን አቅለው ተመልክተዋል ብለዋል፡፡
አሜሪካ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ምትገባው እርሷ እንደምትናገረው ለአለም ሰላምና መረጋጋት ግድ ስለሚላት ሳይሆን ከራሷ ጥቅም አኳያ ትመለከተዋለች፡፡ የአፍጋኒስታን ወቅታዊ ሁኔታም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአፍጋን ለ20 ዓመታት ወታደራዊ ጣልቃ የገባች ቢሆንም ሀገሩን ከመፍረስ አልታደገችውም፡፡ እራሳቸው የዋይታዎስ ሰዎች እንደሚሉት በዚህ ማለቂያ ባልተገኘለት ጦርነቱ ከ40 ሺ በላይ የአፍጋን ንፁሀን ዜጎች ሞተዋል፡፡ 66 ሺ የአፍጋን ወታደሮች ሞተዋል፤ 2448 የአሜሪካ ወታደሮች ሲሞቱ 1144 የኔቶ ወታደሮች ተገለዋል፤ በጦርነቱ 2 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟል፡፡
ይህ ሁሉ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አፍጋኒስታንን ከፅንፈኛ ሀይል አልታደጋትም፡፡ እንደውም ለ20 ዓመታት ያህል በጦርነት ያቆረቆዙትን ሀገር በቃን ሲሉ ሽብርተኛው ቡድን ከአሜሪካ ገር የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ዜጎችን ለጽንፈኛው ቡድን አስረክበው ሀገሪቱን በትነው ጥለው ወጥተዋል፡፡
ለ20 ዓመታት በፀረ-ሽብር ዘመቻ የተንኮታኮተውን ፅንፈኛ ቡድን ታሊባንን ለራሷ እኩይ ተግባር ስትል ደጋግፋ በካቡል አጀግናዋለች፡፡ ዛሬም ውስን ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አሸባሪውን ህወሀት ለራሷ እኩይ አላማ ማሳኪያ ስትል ዳግም ወደ 4 ኪሎ ለማምጣት ጫና ሲያሳድሩ በመስተዋል ላይ ናቸው።
በብዙ መልኩ አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ያልተመሰቃቀለ ሀገር የለም፡፡ ከብረት የጠነከረውን የኢትጵያ የግዛት አንድነት ለመናድም ያልወጣችው፤ ያልገባችበት የውስጥ ጉዳይ የለም፡፡ ከዋሽንግተን ጀርባ የተሸረበውን የማፍረስ ሴራ የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እምብይ ለሀገሬ እንዳሉ አሉ፡፡
(በደረሰ አማረ)