የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደህንነት ኃላፊ ስልጣን ለቀቁ

ሐምሌ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) የአሜሪካ ሚስጥራዊ ደህንነት (secret service) ኃላፊ ኪምበርሊ ቻትል ስልጣናቸውን ለቀቁ፡፡

በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ኃላፊዋ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ከዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ተወካዮች ምክር ቤት ጫና ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡

ኃላፊዋ ስራቸው የሀገሪቷን መሪዎች ደህንነት መጠበቅ ሆኖ ሳለ የትራምፕ የግድያ ሙከራ በመደረጉ ለተፈጠረው የጸጥታ ክፍተት ኃላፊነት እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውሳኔው ከባድ ቢሆንም የሚስጥራዊ ደህንነቱ ዓላማና ፍላጎት ስለሚቀድም ስልጣን መልቀቃቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኃላፊዋ ለዓመታት ሀገራቸውን በታታሪነት በማገልገላቸው አመስግነዋቸዋል፡፡

በቅርቡም አዲስ ሰው በቦታው በቶሎ እንደሚሾሙ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሪፐብሊካን ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን ኃላፊዋ ስልጣናቸውን ከሳምንት በፊት ነበር መልቀቅ የነበረባቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመጨረሻም በመወሰናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት መልዕክት የባይደን መንግስት ደህንነታቸውን በሚገባ እንዳልጠበቀላቸውና ለዲሞክራሲ ሲሉ ጥይት እንዲቀበሉ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ኪምበርሊ ቻትል በአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት ውስጥ ለ27 ዓመታት አገልግለዋል፡፡