የአሜሪካ ኤምባሲ በምርጫ ዘገባ ለሚሳተፉ ጋዜጠኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው

በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ መረጃ በመስጠትና ሁነቶችን በመዘገብ ለሚሳተፉ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በ450 ሺህ ዶላር ወይንም ከ17 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው ጋዜጠኞች በምርጫ ዘገባ ወቅት ሊኖራቸው ስለሚገባው ሃላፊነትና ሚና በአጠቃላይ የሚዳስስ መሆኑ ተጠቁሟል።

ጋዜጠኞች ለመራጮች የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ፣ ተአማኒና ግልጽ መረጃን በማድረስ ደግሞ ሃላፊነታቸውን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ክህሎት ማስጨበት የሚያስችሉ ጉዳዮች በስልጠናው መካተታቸው ተገልጿል።

በምርጫ ዙሪያ የሚዘገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ከስህተት መጠበቅ እንደሚቻል በስልጠናው ከሚዳሰሱ ዋና ሃሳቦች መሃል የተካተቱ ሲሆን ውጤታማ የምርጫ ዘገባዎችን ማከናወን የሚቻልባቸው መንገዶችም እንደሚዳሰሱ ተመልክቷል።

ስልጠናው በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል በጋራ እንደተዘጋጀ ተነግሯል።

ከ500 እሰከ 700 ለሚሆኑ ጋዜጠኞች የሚሰጠው ስልጠናው የ25 ሳምንታት ቆይታ እንደሚኖረውም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።