የአምነስቲና ሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑ ተጠቆመ

ሚያዝያ 6/2014 (ዋልታ) አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰሜኑ ግጭት ዙሪያ ያወጡት ሪፖርት ሚዛናዊ ያልሆነ እና ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጡትን ሪፖርት የካደ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው የአምነስቲና ሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ተጥሰዋል የተባሉ ሰብዓዊ መብቶችን በቅርበት እንደሚመረምረው አስታውቀዋል፡፡

በሳምንቱ በተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎችም በአገር ውስጥ ካሉ የተለያዩ ዲፕሎማቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደተደረገ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ እያደረገ መሆኑንና በዚህ ዙሪያ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ከልክሏል የሚለው መረጃ ሀሰት መሆኑ ለዲፕሎማቶች ግልጽ መደረጉን አንስተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአሜሪካና ካናዳ የዲያስፖራ ተወካዮች ጋር ምክክር አድርገው እስካሁን ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በ#nomore በቃ እንቅስቃሴ ላሳዩት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ሚኒስትሩ በቀጣይ ዲያስፖራው ከአገሩ ጎን በመቆም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ማስተላለፋቸውም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በዋሽንግተንና ሮም ከተሞች ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 የሚቃወሙ የዲያስፖራ ሰልፎች መካሄዳቸውን አምባሳደሩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በደምሰው በነበሩ