የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሳለፈው አቋም ሚዛናዊነት የጎደለው ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሳለፈው አቋም ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ፡፡

አምባሳደሩ ህዳሴ ግድብን አለም አቀፋዊ ጉዳይ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸው ሊጉ ለግብጽና ሱዳን  ወገኝተኝነት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለተለያዩ ሀገራት መንግስታት መረጃ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችም ወደ ተለያዩ ሀገራት እየሄዱ ማብራሪያ እየሰጡ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጋራ በመሆን በለንደን የቡድን ሰባት ሀገራት በሚሰበሰቡበት አዳራሽ አካባቢ  ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል ተብሏል፡፡

በሳምንቱ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ 41 ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከኦማን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን በተመሳሳይ 939 ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ ዓረብያ ተመልሰዋል፡፡

በሳውዲ አረቢያ የመኖርያ ፈቃድ ባላቸው ኢትዮጵያውያን ጭምር እንግልት እየደረሰ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች ወደ ሀገራቸው በፍጥነት እንዲመለሱ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በኡጋንዳ ካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብር አካሂዶ የአንድ ሚሊየን ብር የቦንድ ሽያጭ አድርጓል ተብሏል፡፡

(መስከረም ቸርነት)