የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በኦሮሚያ ክልል ተጀመረ

ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – የዘንድሮ ክልል አቀፍ የዜግነት አገልግሎት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በኦሮሚያ ክልል ተጀመረ፡፡
“ኦሮሚያን እናልብስ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው መርህ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
በክልል አቀፍ የዜግነት አገልግሎት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የአማራ ክልል ርዕሰ መስታዳድር አቶ አገኘው ተሻገር፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመረሃ ግብሩ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ ያለው ይኸው ተግባር ለሌሎች ክልሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ዓመት በአንድ ጀንበር ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ያነሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተያዘው ዓመትም ካለፈው የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ታቅዷል ብለዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያን እየተፈታተኑ ያሉ ኃይሎችን ለማሸነፍ መላው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መቆም እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል፡፡
(በሚልኪያስ አዱኛ)