የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄደ

ነሐሴ 23/2013 (ዋልታ) – “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄደ።

መርሃ ግብሩን የግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን፣ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር፣ የትራንስፎርሜሽናል ሙዚቃና ማስታወቂያ ድርጅት እና ምዕራፋ ፕሮዳክሽን አሰናድተውታል።

የቢሾፋቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለምፀኃይ ሽፈራው፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና ትብብር የብልጽግና ከፍታዋን እንድትላበስ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ ወደ ቢሾፍቱ ለመጡት ሁሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፤ በኢትዮጵያን እናልብስ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ላይ በመገኘት ለአገሯ አሻራዋን በማኖሯ ደስተኛ መሆኗን ገልፃለች።

አረንጓዴ አሻራ ሲታሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ይታሰባል፤ በመሆኑም የአካባቢ ደህንነትን መጠበቅ ለነገ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ይገባል ብላለች።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተው ለኢትዮጵያ አረንጓደ አሻራቸውን አሳርፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።