የአሸባሪው ህወሃትን ወረራ ከጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሆን ሁሉም ሊመክተው ይገባል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ነሐሴ 02/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሃት እያካሄደ ያለውን ግልጽ ወረራ ለመቀልበስ ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ሊፋለመው እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።

በባህር ዳር ከተማ የህልውና ዘመቻ የክተት ጥሪን ተቀብለው ወደ ስልጠና የገቡ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ ተጠባባቂ ሃይሎች ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ አቶ ገዱ ባስተላለፉት መልዕክት “አሸባሪው ህወሓት እያካሄደ ያለው ጦርነት አገሪቱን ለውድቀት ለመዳረግና የህዝብን ክብር ዝቅ ለማደረግ ያለመ ነው” ብለዋል።

ስለሆነም ጦርነቱን ለመመከት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሀገሪቱን ለውድቀት ለመዳረግና የህዝብን ክብር ዝቅ ለማድረግ በግፍ የተከፈተ ጦርነትን መመከት የሚቻለው ፊት ለፊት በመጋፈጥ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

“ወጣቶችም በቁርጠኝነት ተሰልፋችሁ የክልላችሁን ህዝብ እያጎሳቆለ ያለውን የሽብር ቡድን ለመመከት ቁርጠኛ ሆናችሁ መሰለፍ አለባችሁ” ሲሉም አሳስበዋል።

የጥፋት ሃይሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ህብረተሰቡ ለዘመናት ያፈራውን ንብረት እያወደመና እየዘረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

“ይህንን ወረራ መመከትና ለእውነት የሚከፈል መስዋዕትነት የህዝባችንን ክብር ከፍ ለማድረግ፤ የሀገራችንና የህዝባችንን ህልውናም ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው” ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።