የአሸባሪው ሕወሀት ሀይል በኮምቦልቻ ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶች መጨፍጨፉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ

ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓት ኃይል በኮምቦልቻ ከተማ ሰርጎ በመግባት ዛሬ ሌሊቱን ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶችን አሰልፎ መጨፍጨፉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የሽብር ኃይሉ ሰርጎ በገባበት በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የግል እና የመንግስት ሀብቶችን እየዘረፈ እና እያወደመ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በቦርከና ዳዋ ጨፌ አካባቢዎች ሕወሓት እየመጣ ነው በሚል የአሸባሪው ሸኔ ኃይል መንገድ የመዝጋት እና ሌሎች አፍራሽ ድርጊቶችን ለመፈፀም ቢሞክርም በአካባቢው ወጣቶችና በጀግናው መከላከያ ሰራዊት አላማው ከሽፎበታል ብለዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ በክህደት የተፈጠሩበትን የውጊያ መዛነፎች እንደገና በማስተካከል አሁንም ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛልም ተብሏል።

“መንግስት ተዳክሟል፣ ሕወሓት አሸንፎ እየመጣ ነው” በሚል ደሴ ላይ እንደተፈፀመው ሁሉ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ጭፈራ የገቡ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ይህንን አስመልክቶ መንግስት እርምጃ እየወሰደ እንደሆነም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው መግለፃቸውን ኢብኮ ዘግቧል።