የአሸባሪው ሕወሓት ቡድንን ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባ ተገለጸ

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ለውጡን ለመቀልበስ እና ሃገር ለማፍረስ ቢያሴርም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጋራ ተደጋግፈን እንመክተዋለን ሲሉ የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አበበ ማሞ ለዋልታ እንደተናገሩት የሕወሓትን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን ከመቼውም በላይ እንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።

የለውጡ አደናቃፊ ኃይሎች በራሳቸው እና ቅጥረኞችን አሰማርተው የሀገሪቷን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት ኃላፊው በቴፒ የነበረው አለመረጋጋት ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ቴፒ ከተማ አንጻራዊ የሆነ መረጋጋት እየሰፈነባት መሆኑን ጠቅሰው ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዘሪሁን ደሰኖ በበኩላቸው የጁንታውን ሴራ ለማክሸፍ መላው ኢትዮጵያዊ ዝግጅቱን ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚገኙ የቀድሞ ወታደሮች እና የፖሊስ አባላት ወደ ግዳጅ ለመዝመት ጥሪ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ያሉት አስተዳዳሪው ወጣቱ እና ማህበረሰቡ ለመከላከያ ደጀን ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የወረዳዋ ነዋሪዎች በሶስት ዙር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በአይነት እና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው የአሸባሪውን ቡድን ሴራ ለማክሸፍ የህይወት መሰዋእትነትም ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሔለን ታደሰ