የአሸባሪው ሕወሓት ድርጊት በአሜሪካ የተቀነባበረ ነው ሲል እንግሊዛዊው ጸሐፊ ግርሃም ፒብልስ ገለጸ

ኅዳር 19/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓት ድርጊት በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ውስጥ ያሉ አካላትን ጨምሮ በአሜሪካ እና በሌሎች የውጭ ኃይሎች የተደገፈ መሆኑን እንግሊዛዊው ጸሐፊ ግርሃም ፒብልስ ገለጸ፡፡

“ዘ ግሬት ትረስት”ን በማቋቋም በስሪላንካ፣ ኢትዮጵያ እና ህንድ የትምህርት ፕሮጀክቶች ላይ ትልቅ ስራ የሰራው በጎ አድራጊና ጸሐፊ ግርሃም ፒብልስ “በአሜሪካ የተቀነባበረው የኢትዮጵያ ግጭት” በሚል ርዕስ ካውንተር ፐንች በተሰኘ መጽሔት ላይ ሀተታ አስነብቧብ፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ እና እንደገና ሥልጣን ለመያዝ እየሞከረ መሆኑን አንስቷል፡፡

ሙከራው በተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ውስጥ ያሉ አካላትን ጨምሮ በአሜሪካ እና በሌሎች የውጭ ኃይሎች የተደገፈ ነው የሚል እምነትም ያለው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለአገርና ለአካባቢው ጥፋት ነው ሲል ድርጊቱን ኮንኗል፡፡

ግጭቱ የተጀመረው ሕወሓት ጥቅምት 24 በኢትዮጵያ በሰሜን እዛ ላይ በፈጸመው ክህደት መሆኑን ጸሐፊው ጠቅሷል፡፡

ይሁን እንጂ አሜሪካና፣ እንግሊዝ፣ የአውሮፓ ኅብረትና መሰል አገራት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጎን መቆም ሲገባቸው ለአሸባሪው እየወገኑ ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያን መንግሥት በሕገወጥ ለመተካት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጀርባ የባይ ደን አስተዳደር እንዳለ መረጃዎች በሰፊው እየወጡ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ይህን ሁሉ የተቀነባበረ ድርጊት ይክዳሉ ነው ያለው፡፡

እንግሊዛዊው ጸሐፊ የአሜሪካ አስተዳደሮች በ27 ዓመታት የአሸባሪው ሕወሓት የሥልጣን ዘመን የነበራቸው ግንኙነት የፈጠረውን ወያኔን ያለማቋረጥ የመደገፍ ሂደት አሁንም ሙሉ በሙሉ ቀጥለውበታል ነው ያለው፡፡