የአሸባሪው ሸኔ ፍላጎት የኦሮሞን ሕዝብ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፍላጎት መስበር መሆኑ ተገለፀ

ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ያበረው ሸኔ ዋና ዓላማ የኦሮሞን ሕዝብ ፖለቲካዊና ምጣኔሃብታዊ ፍላጎት ማሽመድመድ መሆኑን በሰሞኑ ተግባሩ አረጋግጧል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ።

አስተባባሪ ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በፖለቲካ ኪሳራ አዙሪት ውስጥ የቆየው አሸባሪው ሸኔ ከሽብር ቡድኑ ሕወሓት ጋር የፈፀመው ጋብቻ የፍርፋሪ ፍለጋ እንጂ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ስልታዊነት የሌለው ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ሸኔ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ዕቅድ ሳይሆን ሽብርተኝነት፣ ጥፋትና ደም መፋሰስ ብቻ ነው ብለዋል።

የሸኔ የሽብር ቡድን ፍላጎት ከ50 ዓመት በፊት የነበረ የጫካ ፖለቲካ እሳቤውን በኢትዮጵያና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መጫን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሸኔ እንደ ፖለቲካ ቡድን “ሃምሳ ዓመት ታግለን አልተሳካም፣ ምንም አልሰራንም” ብሎ በማሰቢያው ጊዜ “ሶስት ዙር ተላላኪ” መሆኑን ነው የተናገሩት።

“ፖለቲካው ከተማ ገብቷል ዘምኗል፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ሆኗል፤ የብስለት የጭንቅላት ሆኗል ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር) “በጫካ የሚፈታ ፖለቲካ የለም” ሲሉ አክለዋል።