የአሸባሪዎቹን ቡድን ከማስወገድ ጎን ለጎን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል የአሸባሪዎቹን ቡድን ከማስወገድ ጎን ለጎን የግብርና ልማትን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተመራው ቡድን በኢታንግ ልዩ ወረዳ ኢሊያ ቀበሌ የአርሶ አደሮችን ማሳ ጎብኝተዋል።
በአዲሱ ምዕራፍ የግብርና ልማትን በማጠናከር በምግብ ሰብል ራስን መቻል በአገር ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ኩታ ገጠም የሆኑ የግብርና ልማቶችን ለመደገፍና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተንኩዌይ ጆክ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የክልሉን አየር ንብረት የተላመዱና ዉጤታማ የሆኑ ሰብሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
በኢሊያ ቀበሌ 55 ሄክታር ማሳ በክላስተር ማሽላና በለውዝ መሸፈኑን በዚህም 265 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ቡድን መሪ ደስታ ዘንገታ ናቸው።
የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ማልማት ከተቻለ የክልሉን ብሎም የኢትዮጵያን ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚቻል ከክልሉ ፕሬስ ሴክረታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።