ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) ሴቶችን ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠር የአካባቢያቸውን ሰላም እና የአገርን ሉኣላዊነት ማስጠበቅ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት ያተጋል የተባለ እና “የአሽባሪዎች አገር የማፍረስ ተግባር እና የኦሮሞ ሕዝብ ትግል” የሚል የሴቶች ንቅናቄ ተጀመረ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ፣ በኦሮሚያ ሴቶች ፌደሬሽን እና በኦሮሚያ ሴቶች ሊግ ትብብር የተዘጋጀ የሴቶች ንቅናቄ ውይይት ተካሂዷል።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ሰርካለም ሳኩሜ ውይይቱ አገሪቱ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለሴቶች ግንዛቤ በመፍጥር የአካባቢያቸውን ሰላም እና የአገርን ሉኣላዊነት በማስጠበቅ ዙሪያ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሴቶች ከዚህ በፊት የአገርን ሉኣላዊነት ለማስከበር ወደ መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀል የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የአገርን ሰላም አስጠብቀዋል ያሉት ኃላፊዋ ይሄም ወደ ፊት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ከ10 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን የሚያሳትፈው ውይይቱ “የአሽባሪዎች አገር የማፍረስ ተግባር እና የኦሮሞ ሕዝብ ትግል” በሚል መሪ ሃሳብ በክልል ደረጃ የተጀመረ ሲሆን እስከ ኅዳር 7/2014 በክልሉ ከዞን እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች የሚካሄድ ይሆናል፡፡