የአብሮነት እሴትን በማጠናከር ሊከፋፍሉ የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎችን መታገል እንደሚገባ ተገለጸ

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) ”ኢትዮጵያዊያን የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጠናከር በእምነትና በብሔር ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል” ሲሉ የኢትዮጰያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

በጎንደር ከተማ የተፈጠውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የኅብረተሰቡን የቀጣይ አብሮነት ማስቀጠል የሚያስችል የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ከመላው ዓለም የሚለየን በጠንካራ አብሮነትና መቻቻል ነው።

ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነታችንን ለመሸርሸር ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሁለቱን እምነት ተከታዮች ለመለያየትና ለማጋጨት የሚጥሩ ኃይሎችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።

በእምነቶች መካከል ተቻችሎ አብሮ መኖር ለኢትዮጵያዊያን አዲስ አለመሆኑን ጠቅሰው ይህንም ሁሉም ቤተእምነቶች የሚመሰክሩት ታሪካዊ ሃቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በግጭቱ የፈረሱ ተቋማትን ዳግም በኅብረት ሁነን በመገንባት የተጎዱትን በመደገፍና በማፅናናት በእምነት ሽፋን ወንጀል የፈፀሙ ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል።

በመድረኩ የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሃጅ ኡመር ኢድሪስና የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዱን ጨምሮ 13 የጉባኤው አመራሮች መገኘታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።