ሚያዝያ 14/2015 (ዋልታ) የዜጎችን የአንድነትና የአብሮነት እሴት በማጠናከር ወንድማማችነትን የሚያጸና ቀጣይነት ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያና የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።
የኦሮሚያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛና የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ክልሎቹ የሕዝቦችን አንድነት ማስቀጠል የሚያስችሉ የሕዝብ ግንኙት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ እንደገለጹት ሚዲያ ለሕዝብ አንድነትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት አይተኬ ሚና አለው።
ያም ሆኖ የዲጂታል መገናኛ ዘዴ መበራከት ኃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በማባባስ በሕዝብ መካከል ጥርጣሬ፣ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲኖር ምክንያት እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የቱባ ባህል ባለቤቶችና ታሪካዊ እንዲሁም ባህላዊ የጋራ እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ገልጸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከርና ወንድማማችነትን በማጎልበት አገራዊ አንድነትን ማጽናት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥትም ወንድማማችነት፣ የሕዝብ አንድነትና የአብሮነት እሴቶችን በሚያጎለብቱ ቀጣይነት ያላቸውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንደሚያከናወን ነው ያረጋገጡት።
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ተቀራራቢ ዓላማ በመሰነቅ ለአገር ዘላቂ ጥቅምና ለሕዝብ አብሮነት መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በማስቀጠል አንድነትን ማጽናት እንደሚገባ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ታሪካዊ አንድነት በማስተጋባት የዜጎች አብሮነት እንዲጸና፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ብሎም ብሔራዊ መግባባት ዕውን እንዲሆን አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በዘመናት የታሪክ ውጣ ውረድ በደም የተጋመዱ፣ ፈተናና ድሎችን የተጋሩ እንዲሁም ፈጽሞ የማይለያዩ ሕዝቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህን ታሪካዊ አንድነት ለመሸርሸር ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ገልፀው ክልሉ ይህን ዕኩይ እንቅስቃሴ የሚያከሽፍ ቀጣይነት ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎቹ የህዝቦችን አንድነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት እሴትን አጠናክሮ በማስቀጠል የዲጂታል መገናኛ ዘዴ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲኖር ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።