የአቮካዶ ምርት በማሳደግ ንቅናቄ ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታልሞ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 13/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተጀመረው የአቮካዶ ኢኒሺየቲቭ ወይም የአቮካዶ ምርት የማሳደግ ንቅናቄ በቀጣዩ ዓመት ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አዲሱ አረጋ አስታወቁ፡፡

በክልሉ የአቮካዶ ምርት ውጤታማ በመሆኑ ባለፈው ዓመት ለውጭ ገበያ እንደቀረበም ገልጸዋል፡፡

ድርብ ጥቅሞችን በማስገኘት ላይ ያለው የአቮካዶ ምርት ለአርሶ አደሩ ምግብና የገቢ ምንጭ ሲሆን አረንጓዴ ከባቢን በመፍጠር ውስጥም አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ኃላፊው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የአቮካዶ ዝርያዎች የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማጎልበት እና ለጤና ተስማሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለዚህ ሥራ በሰጠው ትኩረትም ከማምረት ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊ ሃብት እና እድሎቿን ወደ መጠቀም ስትዞር በመሬቶቿ ላይ አዳዲስ ውበቶቿ መስተዋል ጀምረዋል ነው ያሉት።