የአተረጓጎም ልዩነትና ጉራማይሌ ፍትሕን ለማስቀረት በተዘጋጀ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ

ጥቅምት 17/2014 (ዋልታ) በባለሙያዎች መካከል የአተረጓጎም ልዩነት የሚስተዋልባቸው የወንጀል ድንጋጌዎች ዙሪያ በተዘጋጀ የሕግ ማብራሪያ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ፡፡

የሰነዱን ዝግጅት አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደገለጹት ሰነዱ መዘጋጀቱ የፍትሕ ስርዓቱን ውጤታማ፣ ተአማኒና ተገማች በማድረግ ዜጎች ሚዛናዊ ፍትሕ እንዲያገኙ ጉልህ ሚና አለው፡፡

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚጠቁመው ሰነዱ በውይይት ከዳበረና ገንቢ አስተያየቶች ከታከለበት ጉራማይሌ የሆነ የፍትሕ አሰጣጥ እንዳይኖር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው ሰነዱን ያዘጋጁ ባለሙያዎችም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰነዱ በወንጀል ጉዳይ የአተረጓጎም ልዩነት ያለባቸው ድንጋጌዎች፣ አከራካሪ እና ለትርጉም ተጋላጭ ናቸው ተብለው በጥናት የተለዩ የሕግ ድንጋጌዎች ወጥ የሆነ አተረጓጎም እንዲኖራቸው የሚያስችልና ለተመሳሳይ ወንጀል ተመሳሳይ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ለመፍጠር በሚል የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።