ዓለም ላይ ከታዩ የምንግዜውም ምርጥ የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ሯጭ አትሌቶች ቀዳሚ ሥፍራ የተሰጠው ነው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ። በእርሱ የውድድር ዘመን እርሱ ባለበት ማሸነፍን አስቦ ወደ መሮጫ ሜዳ መግባት ለተፎካካሪዎቹ እጅጉን ከባድና ጭንቅ ነው።
ኬኒያዊው ማቹካ የማይረሳውን እና የ1992 የደቡብ ኮሪያ የ10 ሺሕ ሜትር ትንቅንቅ ሲያስታውስ አትሌት ኃይሌ “ሲፈልግ ሙሉ ጊዜውን እንድትመራ ፈቅዶልህ በመጨረሻው ሰዓት ድልህን ይነጥቀሃል” ሲል ገልጾታል፡፡
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በአትሌቲክስ ውድድር 27 ክብረወሰኖችን ሰብሯል፡፡ ለውድድር የማይመቹ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ እንኳን “የይቻላል” መንፈስን ለታናናሾቹ በማጋባትም ይታወቃል።
ሻለቃ ኃይሌ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብዙ ገድል ከሰሩ አትሌቶች መካካል በግንባር ቀደምነት የሚታወቅ ነው፡፡ በሁለት ተከታታይ የኦሎምፒክ ውድድሮች ለህመሙ እጅ ሳይሰጥ ታግሎ በማሸነፍ እና ለሀገሩ ዋጋ በመክፈልም በሁሉም ሰው አዕምሮ “የይቻላል”ን አስተሳሰብ ያኖረ የአሸናፊነት ምልክትም ነው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፡፡
የሞስኮ አሎምፒክ የ5 ሺሕ እና የ10 ሺሕ ሜትር ባለድሉ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የእርሱ ሞዴልና የአትሌቲክስ ህይወት ጅማሮው እንደሆነ የሚናገረው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ለሀገሩ በተለያዩ ውድድሮች ስኬትን አስመዝግቧል፡፡ ኃይሌ ካስመዘገባቸውም ስኬቶች መካከል በህመም ውስጥ ሆኖ ታግሎ ያሸነፈው የኦሎምፒክ ውድድር የሁሉም ነገር መጀመሪያውና ማሸነፍ እንደሚቻል የተገነዘበበት መሆኑንም ያስታውሳል፡፡
በአትላንታ ሳይጠበቅ ልክ እንደቀደሙት ጀግኖች ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያን ያስገኘው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ከ4 ዓመት በኋላ በጉዳት በሲድኒ ኦሎምፒክ እንደማይሳተፍ ያስታወቀበት አጋጣሚም ነበር። በወቅቱ ከህምሙ ለማገገም ደጋግሞ ቢሞክርም ሊሻለው ስላልቻለ በወቅቱ የስፖርት አመራሩ ቡድኑን እንዲያበረታታ በሚል ወደ ስፍራው እንዲያቀና ማድረጋቸውን ተከትሎ በውድድሩ ለመሳተፍ መወሰኑን ይገልጻል፡፡
ለሀገሩ ሲል አመመኝን ደከመኝን የማያውቀው አትሌት ኃይሌ ለሁለተኛ ጊዜ ከህመሙ ታግሎ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በማምጣት በአውስትራሊያ ሰማይ ስር ታሪክን መድገሙ ታሪክ የዘገበው ህያው ገድል ነው፡፡
የ3ኛ የኦሎምፒክ ተሳትፎውን በአቴንስ ያደረገው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ በውድድሩ ሌላኛውን ተተኪ አልጋ ወራሽ ለዓለም አስታዋውቋል ጀግና ቀነኒሳ በቀለን፡፡ በመድረኩ ሁለቱ ያሳዩት እና የነበራቸው ፉክክር ከዚያ አልፎም መተሳሳባቸው የዓለምን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡
ኃይሌ በሲድኒ የተመዘገበው የኦሎፒምክ ድል ሁሌም ተተኪ አትሌቶች እንዲደግሙት አባታዊ ምክሩን የሚለግስ አገር ወዳድ ጀግና መሆኑንም ትውልዱ ያስታውሰዋል፡፡
ኃይሌ ኦሎምፒክን እና የዓለም ሻሚፒዮናን ጨምሮ ለኢትዮጵያ 10 የወርቅ እና 3 ጊዜ የብር 3 ጊዜ ደግሞ የነሀስ ሜዳሊያዎችን ማስገኘት ችሏል፡፡
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የኢትዮጵያ ምልክት ሆኖ በአትሌቲክሱ ዓለም በተለያዩ ርቀቶች በመወዳደር ያስመዘገበው ውጤት ለሀገራችን ብሎም በዓለም በታሪክ ከፍታ ተቀምጦ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡
በሌዊ በለጠ