የአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን የተመለከተ የውሸት ዜና ሊታረም ይገባዋል ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ገለፁ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ በማታለልና በመዋሸት ዜና የሚሰሩበት አዝማሚያ ስር የሰደደ በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አሳሰቡ።
መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባዎቻቸው ሚዛናዊና ኃላፊነት የተሞላባቸው መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት አስተያያት “እውነት የሚሉትን ነገር ለመፈብረክና የሀሰት ዘገባዎችን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን አይጠበቅባቸውም” ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን “ለቅሷቸውንና ጩኸታቸውን” አቁመው ራሳቸውን በማረም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ዘገባዎቻቸውን መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።