የአንጎላ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ዘርፍ ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

ነሃሴ 21/2013 (ዋልታ) – የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የአንጎላ የልዑካን ቡድን አባላትን በመቀበል በሎጅስቲክስ ዘርፍ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

የልምድ ልውውጡ  በኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለውን አሰራር፣ የግሉ ባለሃብት ተሳትፎ፣ የዘርፉ ችግሮችና እየተፈቱበት ያለውን አሰራር  ለመቅሰም ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የማሪታም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮነን አበራ÷ የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ዘርፍ ልምድ ለመለዋወጥ መምጣቱን አመስግነዋል፡፡

የሎጅስቲክስ ዘርፍ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ አስቻይ በመሆኑ  በትኩረት እየተሰራ   ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በጥናት ነቅሶ በማውጣት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፎ ሀገራዊ ሃላፊነት ባለው  ብሄራዊ ምክር ቤት  እየተመራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአጠቃላይ በሎጅስቲክስ አሰራር፣ ችግሮችና የመፍትሄ እርምጃዎች፣ በሞጆ ሎጅስቲክስ ማዕከል ግንባታ፣ የቀዝቃዛ ምርቶች ፕሮጀክት ላይ ገለጻ መደረጉን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው÷ በቀጣይ በሎጅስቲክስ ዘርፍ አብሮ ለመስራትና ለቴክኒካል ኮሚቴ ተጨማሪ ልምድ ከኢትዮጵያ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል፡፡