የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ፣ የባቡር ሀዲድ ማያያዣ እና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ ተጣለ

በኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር መነሻውን አዋሽ 7 በማድረግ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አራት አበይት ክፍሎችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በአዋሽ ሰባት የሚሰራውን የነዳጅ ማቆሪያ ጨምሮ በቱርኩ ያፒ መርከዚ የተጀመረውን የአዋሽ ኮምቦልቻ፣ ወልደያ የባቡር መስመር ከአዲስ አበባ ደዋሌ መስመር ጋር ማያያዝ፣ የአዲስ አበባ ሜኤሶ የባቡር መስመርን ከአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ ጋር ማያያዝ፣ የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና በአዋሽ ሁለት ፌርማታ መገንባት መሆኑ ተነግሯል።

በፕሮጀክት ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ኢድሪስ በአገሪቱ ያለውን የነዳጅ እጥረት በፍጥነት ለመፍታት አማራጭ መንገድ የመጓጓዣ ዘዴውን ማዘመን መሆኑን ገልፀው፣ ይህ የባቡር ሀዲድ እና የነዳጅ ማጠራቀሚያ ግንባታ በአካባቢው ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፋሎች ሰፊ የስራ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።

በ2 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በአገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እምርታ ያመጣል ያሉት የምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለነዳጅ አቅርቦት ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ታወጣለች ይህንንም ከፍተኛ የሆነ ወጪ ለመቀነስና አዲስ የባቡር ትራንስፓርት ዘዴ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ያሉት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ኃ/ማርያም አዲስ የሚገነባው የባቡር ሀዲድ ወጪ ቆጣቢ እና ፈጣን በሆነ መልኩ ነዳጅ ለማመላለ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጧሃ መሀመድ በበኩላቸው፣ በክልሉ ያሉ የወሰን እና ድንበር ማስከበር ሂደቶችን ምቹ በማድረግ የተጀመረው ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፓሬሽን የሚከናወን ሲሆን፣ የቻይና ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንት ኮርፖሬሽን እንደሚሳተፍበት ለማወቅ ተችሏል።
(በቁምነገር አህመድ)