የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ግንቦት 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ደረሱ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራው እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማልን ያካተተው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን በቤት ልማት ዙሪያ ባካሄደው ምክክር ነው የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባል የሆኑት ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል አቻ ከሆነው ተቋም ከአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ሰፊ ምክክርና ውይይት አድርገዋል፡፡

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ በመንግስት መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት የሚገነባቸውን ቤቶች ከ30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ከገበያው የዋጋ ቅናሽ ያላቸውን ቤቶች ለአገሪቱ ዜጎች በሽያጭ እያቀረበ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከመንግስት የሚያገኘውን መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ገበያ ለመረጋጋት ለሚገነባቸው ቤቶች ግንባታ የሚያውል ሲሆን ያገኘውን የበጀት ድጋፍ ለመንግስት የመመለስ ግዴታ የሌለበት ተቋም እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ላለው ጥረት የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ያለውን ሰፊ ልምድ ለፌዴራል ቤቶች የሚጋራ መሆኑም ተገልጿል።

ሁለቱ ተቋማት በቤት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ጉዳዮች ላይ ስምምነት በመደረሱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲን ልምድና ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም መገለጹን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቀደሞው ኪራይ ቤቶች የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱን ጠንካራ መንግስታዊ የሪል ስቴት ካምፓኒ ለመሆን በሚያስችለው አግባብ እየደረጀ ሲሆን የሪል ስቴት ገበያው እንዲረጋጋ የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑም ተገልጿል።