መጋቢት 16/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና በአስፈፃሚው አካል መካከል የእቅድ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተከናወነ፡፡
የስምምነት ፊርማው ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልቃድር በተገኙበት መካሄዱ ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕዝቡን ውክልና ሥራዎችና አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር በአግባቡ መሥራት እንዲያስችለው ቋሚ ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ምክር ቤቱ አስፈፃሚውን አካል የመከታተልና መቆጣጠር ስልጣኑን ተግባራዊ ለማድረግ ብሎም የተጠያቂነትን ሥርዓት ለማስፈን እንዲረዳው በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና በአስፈፃሚው አካላት (የቢሮ ኃላፊዎች) መካከል የተቋማቱን ዕቅድ መሠረት ያደረገ የስምምነት ፊርማ ነው የተካሄደው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ዛሬ የተካሄደው ስምምነት ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓላማ ያነገባና ስራን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነው፡፡
ምክር ቤቱና ሕዝባችን የጣለሉብንን ኃላፊነት በተሟላ አግባብ እንድንፈጽም የሚያስችል የተጠያቂነት ሥርዓትን ከንግግር ባለፈ መሬት ላይ ለማውረድ የሚረዳ፤ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንድናቀርብ የሚያስችለንም ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች አስፈፃሚውን አካል በየጊዜው በመከታተል በመቆጣጠርና በመደገፍ የከተማዋን ዕድገት፣ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ሊሠሩ እንደሚገባ መናገራቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!