ሐምሌ 2፣ 2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በክረምቱ የተለያዩ የበጎ ተግባር አገልግሎቶችን ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ በ2013 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ያደረገውን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን በሰጡት መግለጫ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስፖርት መሰረታዊ ስልጠና፣ ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ የችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በክረምቱ የስፖርት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸው የፊታችን እሁድ በይፋ ይጀመራል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ በተለያዩ የስፖርት አይነቶችና ፌስቲቫሎች በመስቀል አደባባይ የሚጀመር ሲሆን በእለቱ የደም ልገሳ የቤት እድሳትም ይከናወናል ብለዋል አቶ በላይ።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የእርስ በእርስ ትስስርና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የክረምት የስፖርት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ”በአረንጓዴ አሻራ ያበበች፣ በሰብዓዊነት ላይ የተገነባች አዲስ አበባን እንፈጥራለን ” በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል።
የአዲስ አበባ ከተማ የክረምት የስፖርት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ከሐምሌ 4 ቀን 2013 እስከ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከናወን ይሆናል።
በዚህ መርሃ ግብር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የስፖርት ቤተሰቦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንደሮው ክረምት 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት እቅድ መያዙን ኢዜአ ዘግቧል።