የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ የመሠረታዊ ፓርቲ ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ሁሉም አባላት የሚሳተፉበትና በቅርቡ የሚካሄድ ጉባዔ አካል የሆነ የመሠረታዊ ፓርቲ ኮንፈረንስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ዓለሙ በሰጡት መግለጫ በ1860 መሠረታዊ ፓርቲ እየተከናወኑ ያሉ ኮንፈረንሶች በዋናነት ከጉባኤ ዝግጅት ጋር የሚያያዙ ሲሆን የጉባኤ ተሳታፊዎችም የሚመርጡበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይ ለሚኖረው የፓርቲ ጉባኤ የሚያስቀምጣቸውን መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ቅድመ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል።
የኮንፈረንሱ አላማ በፓርቲው ውስጥ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ደረጃ በሚመለከት ያጋጠሙ እና እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን መሻገር የሚያስችል ብቁ አመራርና አሠራር ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
የጉባኤው “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ እንደሆነ ከአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለከታል።