የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሁሉም ክፍለ ከተሞች አዳዲስ አመራሮች መመደባቸውን አሳወቀ

ነሐሴ 17/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሁሉም ክፍለ ከተሞች አዳዲስ አመራሮች መመደባቸውን አሳውቋል፡፡

ምክር ቤቱ የክፍለ ከተማ ስራ አመራሮች ምስረታና የትውውቅ መርሃ ግብርም አካሂዷል፡፡

አዳዲስ አመራሮቹ የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት ማስጠበቅ፣ ፍትህና ሰላም ማስፈን እንዲሁም  በትብብር መስራት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባል ሼክ አብዱልሃሚድ አህመድ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም ከአመራሮቹ ጋር መስራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

የአመራሮቹ አመራረጥም መስፈርት የወጣለት ሲሆን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ፣ በትምህርት ደረጃቸው የተሻሉና በመልካም ስራቸው የተመሰገኑ እንዲሁም ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

በተስፋዬ አባተ