የአዲስ አበባ የመንግስት ት/ቤቶች በይፋ ትምህርት መስጠት ጀመሩ

በአዲስ አበባ ከተማ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ዛሬ በይፋ ጀመሩ፡፡
የትምህርት አጀማመርን ለመመልከት ዋልታ ቴሌቪዥንም በጆን ኦፍ ኬኔዲ ትምህርት ቤት የተገኘ ሲሆን፣ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ናደው ባዩ ትምህርት ቤቱ በኮቪድ-19 ምክንያት በድጋሚ እንዳይዘጋ ሁሉም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውና ዛሬ የተጀመረው የመማር ማስተማር ሂደት በስኬት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
የጆን ኤፍ ኬኔዲ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎቹን መደበኛ ትምህርት አስጀምሯል።
በትምህርት ማስጀመር ወቅት ከ9 ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ለተመለሱት ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመምህራን የተሰጠ ሲሆን፣ የእጅ መታጠብ ሂደትን ጨምሮ ማስክ ማድረግ እና ርቀትን መጠበቅ ግዴታ ስለመሆኑም ግልፅ ተደርጎላቸዋል፡፡
የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሊያ ከ9 ወራት ቆይታ በኋላ ትምህርት ቤት በመከፈቱ የተሰማትን ደስታ በመግለጽ፣ “ትምህርት ቤቴ በድጋሜ እንዳይዘጋብኝ ራሴን እና የትምህርት ቤት ጓደኞቼን ከኮሮና ቫይረስ እጠብቃለሁ” ብላለች፡፡
ከ9 ወራት በኋላ ተማሪዎቿን ያገኘችው መምህርት ቅድስት አይቸግረው በበኩሏ፣ የወላጆችን ትልቅ እምነት ስለተሸከምን ተማሪዎቻችንን ከማስተማር ባሻገር ለጤንነታቸው መጠበቅ ትኩረት እንሰጣለን ስትል ገልጻለች።

(በቁምነገር አህመድ)