የካቲት 11/2013 (ዋልታ) – የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን የማንቂያ ደወል ነው ሲሉ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒታ ሞርጋን ተናገሩ፡፡
የአድዋ ድል አፍሪካውያን በአንድ ላይ ሲሆኑ በሚፈጥሩት ጠንካራ ሕብረት ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉም ማሳያ እንደሆነ አምባሳደሩ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን ድል የተነቃቁት አፍሪካውያን የራሳቸውን ነፃነት እውን ለማድረግ እንዲታገሉ ከማስቻሉ ባሻገር አፍሪካውያን በአንድ ላይ ሲሆኑ ሀይል እንዳላቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን በአንድ ቀን ካስመዘገበች አፍሪካውያን በአንድነት ችግሮቻችንን ህብረትና አንድነታችንን በማጠናከር የሌሎች አገራትን ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ፒታ ሞርጋን የቅኝ ገዢዎች ያሰመሩትን የልዩነት ድንበር ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸው የአፍሪካን ህብረት ሰንደቅ አላማ አንዱን አገር ከአንዱ የሚለይ አንድም መስመር የለውም ይህም አንድነትን ያመላክታል ሲሉ አክለዋል፡፡
የአፍሪካን ህዳሴን እውን ለማድረግ በሰላም ግንባታ፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር በአፍሪካ ለአፍሪካውያን ነጻ እንቅሳሴን መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካውያን የእርስ በእርስ ሽኩቻን ወደ ኋላ ትተን ለእድገት እና ለብልጽግና ህብረታችንን በማጠናከር የአፍሪካን ትልቁ የልማት መሪ እቅድ የሆነውን አጀንዳ 2063 ማሳካት አለብንም ብለዋል፡፡
አምባሳደር ጄምስ ፒታ ሞርጋን እንኳን ለ125ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ በማለት የድሉ ጀግኖች ያወረሱትን ማንነት አፍሪካውያን ድህነትን ድል በማድረግ መድገም እንዳለባቸውም አስሳስበዋል፡፡
(በትዝታ መንግስቱ)