የአገልግሎት አሰጣጥ ፖሊሲው ሊቀየር መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 12/2013 (ዋልታ) – ከ20 ዓመታት በላይ የቆየው የአገልግሎት አሰጣጥ ፖሊሲ በዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ጉዳዮች ምክንያት ሊቀየር መሆኑ ተገለጸ፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን  ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ ሀገርን ሊያሻግር የሚችል ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ የአገልጋዩን እና የተገልጋዩን ችግር ሊቀርፍ በሚችል መልኩ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት አገልግሎት በውጤትና በተጠያቂነት የታጀበ መሆን አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ አገልግሎት አሰጣጥ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳታል ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚለዋወጠውን የተገልጋይን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት ያስፈልጋልም ተብሏል።

በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ሁሉም ክልሎቸና የሚመለከታቸው አካላት  ሀሳቦችን አንስተዋል።

ሁሉም አገልጋይ በሙያው የሚጠበቅበትን ካደረገ በፈጠራ የተሞላ ትውልድ መፍጠር እንችላለን ያሉት ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ፣ ለክልሎች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን የሚያዘምን ፖሊሲ ሊኖራቸው ይገባል ለዚህም ደግሞ ሌሎች ፖሊሲዎችን መቃኘት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በበኩላቸው፣ አገልግሎት ፈላጊው በግልፅ ቅሬታ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፣ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገር በቀል እሴትን በማብዛት ተጠያቂነት ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል።

ዜጎችን መሰረት ያደረገ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ሀገሪቱ በቀጣይ ልትገነባ ያሰበችውን ለውጥ ለማሳካት የአገልግሎት አሰጣጥን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የማስፈፀሚያ ህጎቹ አንድ ላይ ተሰናስነው የሚቀርቡ እንደሚሆኑም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

(በአካሉ ጵጥሮስ)