የአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሥራውን ጀመረ

ታኅሣሥ 25/2014 (ዋልታ) በአሸባሪዎቹ ትሕነግ እና ሸኔ ቡድኖች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የትምህርት ቤቱ ሱፐርቫይዘር ማሙሽ ሲከፋኝ ትምህርት ቤቱ አንጋፋና በክልሉ ካሉ ውጤታማ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በጥፋት ኃይሎች በተደጋጋሚ የጉዳት ሰለባ በመሆኑ በትምህር ቤቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡
የትምህርት አስተዳደሩ በደረሰው ጉዳት ተስፋ ሳይቆርጥ የአጥፊ ቡድኖቹ እቅድ እንዳይሳካ ትምህርት ለማስጀመር ከመምህራን ጋር ተግባብቶ የማስተማር እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ መምህራን በበኩላቸው ካለው ጫና ተላቀው በቀረው ትንሽ የትምህርት ግብዓት የመማር ማስተማር ሥራውን በተሻለ የሥነ-ልቦና ዝግጅት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ቤቱ መምህራን ትምህርት ቤቱን ከማጽዳት ጀምሮ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ እንዲመጡ ሥነ-ልቦናቸውን የመገንባት ሥራም እየሰሩ እንደሚገኙ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
የተለያዩ አካላት ችግሮቹን መጥቶ ከመመልከት በዘለለ የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚችለውን ድጋፍ እዲያደረግ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጠይቋል፡፡