“የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በማንነቱ ለመጣ ምህረት የለውም” አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በማንነቱ ለመጣ ወራሪ ኃይል ምህረት እንደሌለው በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ገለጹ።
አሸባሪው የሕሕሓት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸመው ወረራም ኢትዮጵያዊያንን ለዳግም ጭቆና የመዳረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሕወሓት ወራሪ ኃይል ገብቶ በነበረባቸው የአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አድርሷል።
ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የሕዝብ ንብረቶችን አውድሟል።
የሽብር ቡድኑ እንደ ግመል፣ ፍየል እና የመሳሰሉ የቁም እንስሳትን ጭምር በመግደል በአፋር ወገኖች ላይ የጭካኔ በትሩን ማሰረፉ ተነግሯል።
የቡድኑ ወራሪ ኃይል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመፈጸም በርካታ ንጹኃን ዜጎችን ለህልፈት ሲዳርግ ከ300 ሺሕ በላይ ወገኖችን ደግሞ ከቀያቸው በማፈናቀል ለከፋ ሰብኣዊ ጉዳት መዳረጉ ተጠቅሷል።
አምባሳደር ሀሰን አሸባሪው ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸመው ወረራ የቡድኑ የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት የመዳፈር ድርጊቱ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑን አስነዋሪ ወረራ ለመቀልበስም የአፋርና የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን እየቀለበሱት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአፋር ግንባር በክልሉ ፕሬዝደንት አወል አርባ የሚመራው ኮማንድ ፖስት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።