የአፋር እና ሶማሌ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተስማሙ

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የአፋር ክልል እና የሶማሌ ክልል በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት አደረጉ።

ባለፉት ጊዜያት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በእርቅና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነው ስምምነት ያደረጉት፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ በጋራ በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ አልፎ አልፎ እየተነሳ ያለውን ችግር ከስር መሰረቱ ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

ግጭቶች ተመልሶ እንዳይነሱና የሰው ሕይወት መጥፋት ስለሌለበት ከስምምነት በመድረሳቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱ ዘለቂ ሰላም በአዋሳኝ አካባቢዎች እንዲኖር ክልሉ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

የግጭቱ መነሻ የሆኑ ጥያቄዎች በህጋዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ብቻ እንዲመለሱ በፌዴራል ባለድርሻ አካላት የሚመራ መሆኑን ገልፀው ሰላም እንዲመጣ እንሰራለን ነው ያሉት።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የታዩ አለመግባባቶችን ወደ ጎን በመተው አሳታፊ የሆነ የህዝብ ውይይቶች በማድረግ ልዩነቶችን በውይይት ብቻ ለመፍታት ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል።

ግጭቶችን በመተው መግባባት ላይ የተደረሱባቸውን ጉዳዮች በመለየት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውቀዋል።

በግዛቸው ግርማዬ